1 Kings 19

ኤልያስ ወደ ኮሬብ ኰበለለ

1አክዓብ በዚህ ጊዜ፣ ኤልያስ ያደረገውን በሙሉ፣ ነቢያቱንም ሁሉ እንዴት በሰይፍ እንዳስገደላቸው ለኤልዛቤል ነገራት። 2ስለዚህም እርሷ፣ “ነገ በዚህ ሰዓት ያንተንም ነፍስ ከእነዚያ እንደ አንዱ ነፍስ ሳላደርጋት ብቀር አማልክት እንዲህ ያድርጉብኝ፤ ከዚህ የባሰም ያምጡብኝ” ስትል ወደ ኤልያስ መልእክተኛ ላከች።

3ኤልያስም ፈርቶ
ወይም ኤልያስ አይቶ ተብሎ ሊተረጐም ይችላል
ስለ ነበር፣ ሕይወቱን ለማትረፍ ሲል ሸሸ። በይሁዳ ምድር ወዳለችው ወደ ቤርሳቤህ እንደ መጣም አገልጋዩን በዚያ ተወው፤
4በምድረ በዳም ውስጥ የአንድ ቀን መንገድ ተጓዘ፤ ወደ አንድ ክትክታ ዛፍ እንደ መጣም፣ ከሥሩ ተቀምጦ፣ ይሞት ዘንድ “እግዚአብሔር ሆይ፤ በቅቶኛል፤ እኔ ከቀደሙት አባቶቼ አልበልጥምና ነፍሴን ውሰዳት” ብሎ ጸለየ። 5ከዚያም ከዛፍ ሥር ተጋደመ፤ እንቅልፍም ወሰደው።

በድንገትም አንድ መልአክ ነካ አደረገውና፣ “ተነሥና ብላ” አለው።
6ዘወር ብሎ ሲመለከትም፣ እነሆ፣ በፍም የተጋገረ ዕንጐቻና አንድ ገንቦ ውሃ ከራስጌው አገኘ፤ ከበላና ከጠጣም በኋላ ተመልሶ ተኛ።

7 የእግዚአብሔርም መልአክ እንደ ገና መጥቶ ነካ አደረገውና፣ “ሩቅ መንገድ ስለምትሄድ ተነሥና ብላ” አለው። 8ስለዚህም ተነሥቶ በላ፤ ጠጣም፤ በምግቡም ብርታት አግኝቶ ወደ እግዚአብሔር ተራራ ወደ ኮሬብ እስኪደርስ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ተጓዘ፤ 9በዚያም ወደ አንዲት ዋሻ ገብቶ ዐደረ።

እግዚአብሔር ለኤልያስ ተገለጠለት

የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እርሱ መጣ፤ “ኤልያስ ሆይ፤ እዚህ ምን ታደርጋለህ?” አለው።

10እርሱም፣ “እኔ ለሰራዊት ጌታ ለእግዚአብሔር እጅግ ቀንቻለሁ፤ እስራኤላውያን ኪዳንህን ትተዋል፤ መሠዊያዎችህን አፍርሰዋል፤ ነቢያትህንም በሰይፍ ገድለዋልና። የቀረሁት እኔ ብቻ ነኝ፤ አሁንም እኔን ለመግደል ይፈልጋሉ” አለ።

11 እግዚአብሔርም፣ “እግዚአብሔር በዚያ ያልፋልና ወደ ተራራው ወጥተህ በእግዚአብሔር ፊት ቁም” አለው።

ከዚያም ታላቅና ኀይለኛ ነፋስ ተራሮቹን ሰነጣጠቀ፤ ዐለቶችንም በእግዚአብሔር ፊት ብትንትናቸውን አወጣ፤ እግዚአብሔር ግን በነፋሱ ውስጥ አልነበረም፤ ከነፋሱም ቀጥሎ የምድር መነዋወጥ ሆነ፤ እግዚአብሔር ግን በምድር መነዋወጡ ውስጥ አልነበረም።
12ከምድር መነዋወጡም ቀጥሎ እሳት መጣ፤ እግዚአብሔር ግን በእሳቱ ውስጥ አልነበረም፤ ከእሳቱም ቀጥሎ ለስ ለስ ያለ ድምፅ ተሰማ። 13ኤልያስም ይህን ሲሰማ፣ ፊቱን በመጐናጸፊያው ሸፍኖ ወጣና በዋሻው ደጃፍ ቆመ።

ከዚያም፣ “ኤልያስ ሆይ፤ እዚህ ምን ታደርጋለህ?” የሚል ድምፅ ሰማ።

14እርሱም፣ “እኔ ሁሉን ለሚችል ጌታ ለእግዚአብሔር እጅግ ቀንቻለሁ፤ እስራኤላውያን ኪዳንህን ትተዋል፤ መሠዊያዎችህን አፍርሰዋል፤ ነቢያትህንም በሰይፍ ገድለዋልና። የቀረሁት እኔ ብቻ ነኝ፤ አሁንም እኔን ለመግደል ይፈልጋሉ” አለ።

15 እግዚአብሔርም እንዲህ አለው፤ “በመጣህበት መንገድ ተመልሰህ ወደ ደማስቆ ምድረ በዳ ሂድ፤ እዚያ ስትደርስም አዛሄልን በሶርያ ላይ እንዲነግሥ ቅባው። 16እንዲሁም የናሜሲን ልጅ ኢዩን በእስራኤል ላይ እንዲነግሥ ቅባው፤ ደግሞም ነቢይ ሆኖ በእግርህ እንዲተካ የአቤል ምሖላን ሰው የሣፋጥን ልጅ ኤልሳዕን ቅባው። 17ከአዛሄል ሰይፍ ያመለጠውን ኢዩ ይገድለዋል፤ ከኢዩ ሰይፍ ያመለጠውን ደግሞ ኤልሳዕ ይገድለዋል። 18እኔም ጕልበታቸው ለበኣል ያልተንበረከከውንና አፋቸው ምስሉን ያልሳመውን ሰባት ሺሕ ሰዎች በእስራኤል አስቀራለሁ።”

የኤልሳዕ መጠራት

19ስለዚህ ኤልያስ ከዚያ ተነሥቶ ሲሄድ፣ የሣፋጥን ልጅ ኤልሳዕን ዐሥራ ሁለት ጥማድ በሬ አውጥቶ ራሱ በዐሥራ ሁለተኛው ጥማድ በሬ ሲያርስ አገኘው። ኤልያስም ወደ እርሱ መጥቶ መጐናጸፊያውን በላዩ ጣለበት። 20ከዚያም ኤልሳዕ በሬዎቹን ትቶ ኤልያስን ተከትሎ እየሮጠ፣ “አባቴንና እናቴን ስሜ እንድሰናበታቸው ፍቀድልኝ፤ ከዚያም እከተልሃለሁ” አለው።

ኤልያስም መልሶ፣ “እኔ ምን ያደረግሁህ ነገር አለ? ልትመለስ ትችላለህ” አለው።

21ስለዚህም ኤልሳዕ ትቶት ተመለሰ። ሁለቱን በሬዎቹን ወስዶ ዐረደ፤ የዕርሻ ዕቃውን አንድዶ ሥጋቸውን በመቀቀል ለሕዝቡ ሰጠ፤ እነርሱም በሉ። ከዚያም ኤልያስን ለመከተል ሄደ፤ ረዳቱም ሆነ።

Copyright information for AmhNASV